የሲዳማ ህዝብ ዘመን መለወጫ - ፊቼ ጫምባላላ እና እሴቶቹ

የሲዳማ ህዝብ ዘመን መለወጫ - ፊቼ ጫምባላላ እና እሴቶቹ

ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዝሀ ባህል፣ እምነትና ማንነት ባለጸጋ ናት፡፡ ሁሉም ብሔሮች የጋራና የየራሳቸው የሆነ ባህልና ትውፊት አላቸው፡፡ የሲዳማ ብሔርን ከሌሎች ጋር የሚያመሳስለው እንዲሁም የእራሱ መገለጫ የሆነ ልዩ ባህልና ትውፊት ያለው ህዝብ ነው፡፡ ከነዚህ መገለጫዎች መካከል ፊቼ-ጫምባላላ አንዱ ነው፡፡ ፊቼ ጫምባላላ የሲዳማ ህዝብ በጨረቃና ከዋክብት ዑደት ላይ ተመስርቶ የዘመን ቀመር አበጅቶ በድምቀት የሚያከብረው የዘመን መለወጫ ታላቅ በዓል ነው፡፡ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ ጨምበላላ ከጥንት ጀምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ ከነሙሉ ክብሩ ዛሬ ላይ የደረሰ ደማቅና የዓለም ቅርስ የሆነ በውስጡ አያሌ ለሰው ልጅና ለተፈጥሮ ጠቃሚ እሴቶችን ያቀፈ ድንቅ ባህል ነው፡፡

ፊቼ ጫምባላላ ከዘመን መለወጫ በዓልነቱ ባሻገር የሲዳማ ህዝብ ጥልቅ የሆነ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊና የአኗኗር እሴቶች መገለጫ የሆኑ ሰላምን፣ መከባበርን፣ ፍቅር፣ አብሮ መኖርን፣ መቻቻልን፣ ልማትን፣ እርቅን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማክበር እሴቶችን ያዘለ ድንቅ በዓል ነው። ከእነዚህ  መካከል  አንኳር  አንኳሮቹ፡-

የሰላም ተምሳሌትነት

ፍቼ ጫምባላላ የሰላም በዓል ነዉ። ሰላም የፍቼ ጫምባላላ አስኳሉ ነዉ። ህዝቡ ሰላም የሚመኝበት፤ ለሰላም የሚፈላለግበት በዓል ነዉ። ስለዚህ ጭሜሳዎች (ሽማግሌዎች) በዓሉ ከመምጣቱ አንድ ወር አስቀድመዉ ኡሱራ የተሰኘዉን ፆም በመግባት (በመፆም) ለሀገር፥ ለህዝቡና ለከብቶች ሰላም እንዲሰፍን ወደ ማጋኖ (ፈጣሪ) ይማፀናሉ። በፍቼ ጫምባላላ በዓል የተጣሉ ሰዎች ይታረቃሉ፤ ያለ ዕርቅ ወደ አዲሱ ዓመት አይታለፍም። ቤተሰብ ወይም ዘመድ የሞተበት ሰዉ ጥዳዉን (ሀዘኑን) ለመርሳት ቅቤ የሚቀባበት በዓል ነዉ። ከብቶች የማይታረዱበት፥ የዱር እንስሳት የማይታደኑበት፥ የማይሰደዱበት በዓል ነዉ። ልጆች ጥፋት ቢያጠፉ እንኳን የማይቀጡበት (ቃላዊም ሆነ ኣካላዊ) ለሰዉ ልጅ፥ ለእንስሳትና ለተፈጥሮ ሁሉ ሰላም እንዲሆን የሚጠነቀቅበት ታላቅ በዓል ነዉ።

ብዙኃነትን ከማቀፍና ከእኩልነት አንፃር

በፍቼ ጫምባላላ ሁሉም ሰዉ እኩል ይሳተፋል (ወንድ፥ ሴት፥ ሀብታም፥ ድሃ፥ ልጅ፥ አዋቂ  ያለ አንዳች ልዩነት) ማንኛዉም ሰዉ የበዓሉ ታዳሚ የመሆን መብት አለዉ። ሰዎች በህብረት ወደ ጉዱማሌ ይወጣሉ። የፍቼ ጫምባላላ ህብረ ዜማ ቄጣላ እንዲሁም ፋሮ እና ሆሬ በህብረት የሚደምቁ ናቸዉ። ፍቼ ጫምባላላ ለከብቶችም ጭምር ትልቅ ቦታ የሚሰጥበት በዓል ነዉ። ከብቶች ከሰዎች ጋርሁሉቃ ይሾልካሉ። የሁሉቃ ሥነ ሥርዓት በእርጥብ ቀርከሃ ወይም ሀገር በቀል እንጨት ተሰርቶ ሰዎችና ከብቶች የሚሾልኩበት ከአሮጌ ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት የመግባት ተምሳሌት ነዉ። ያለዉ ለሌለዉ የሚለግስበት፥ ሁሉም ያለ ልዩነት የሚደሰትበት ሁሉን አቀፍ በዓል ነዉ።ህፃናትና ሴቶች መብት ረገድ ዓለም አሁን ነቅቶ ‹‹የእኩልነት መብትና የፆታ ጉዳይ›› እያለ ከመስበኩ አስቀድሞ ሲዳማ በፊቼ ጫምባላላ አክብሮቱን ሲያሳይ ብዙ አመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡

ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር

ፍቼ ጫምባላላ ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋፅአ አለዉ። ዛፍ አይቆረጥም። የጉዱማሌ ወይም ፊቼ የሚከበርበት አደባባይ ዛፎች ቅርንጫፋቸዉ አይነካም። የግጦሽ ሣር ተከልሎ ያድጋል። አደን ስለማይታደን ሁሉም ተፈጥሮ ያርፋል። አካባቢን የመጠበቅ ባህላዊ መንገዱ ዓለማችንን እየተፈታተነ ላለው ለአየር ለውጥ እና የሚያስከትለውን ጉዳት ከመቋቋም አንጻር ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ 

ቋንቋና ባህልን ከማበልፀግ አንፃር

ፍቼ ጫምባላላ የሲዳማን ቋንቋ (ሲዳሙ ኣፎን) በንግግርም ሆነ በፅሁፍ የማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለዉ። በንግግር፦ ሬዲዮ፥ ቴሌቭዢን፥ ስነ ቃል  በፅሁፍ፦ ጥናታዊ ፅሁፎች፥ መፅሔቶች፥ ጋዜጦች፥ መጽሐፍት፥ በራሪ ፅሁፎች፥ ለቋንቋ እድገት የራሳቸዉ የሆነ አስተዋፅኦ አላቸዉ። ብዙ አድማጭና ተመልካች ብሎም አንባቢ በዚሁ በዓል ላይ ስለሚገኝ  ሀገራዊ መልዕክት በቀላሉ ከዳር እስከዳር ለማስተላለፍም ይቻላል። ባህላዊ ምግብ (Buurisame)፣ ባህላዊ  ልብስ (የወንድ፥ የሴት፥ የልጆች፥ የወጣቶች፥ የአዋቂ፥ የአርበኛ ወዘተ)፣ ጌጣጌጥባህላዊ የፀጉር አሠራር (በዚህ በዓል ጎልቶ ይታያል)፣ እነዚህ ባህል ሳይከለስ፣ ሳይበረዝ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲቆይ ከማድረግም ባሻገር የበዓሉ ድምቀትም ነዉ።

ማጠቃለያ ፍቼ በዘመነ ሉላዊነት

ፊቼ ጫምባላላ ስለ ሰላም የሚሠጠው ከፍ ያለ ቦታ በሰው ልጆች ላይ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ስጦታዎ ጭምር የሠላም አየር እንዲነፍስ የሚያደርጉ እሴቶች በውስጡ የያዘ ነው። ይህ እሴት የሲዳማ አባቶችና እናቶች የጊዜ እርዝማኔ፣ የሁኔታዎች መለዋወጥ፣ የዓለም ስርዓት ለውጥ፣ የመንግስታት መሻር፣ ጭቆና፣ አፈና፣ መሰደድ እና መገፋት ሳይበግራቸው ሳይበረዝና ሳይከለስ ጠብቀው ከሲዳማ አልፈው ለሀገራችን እንዲሁም ለዓለም ያወረሱት ፍቼ ጨምበላላ እንደማንኛውም ሀገር በቀል እውቀትና እሴት በሉላዊነት መፈተኑ አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም እሴቱ እንደ ቀደምት አባት እናቶች የዛሬው ትውልድም በሉላዊነት ተጽዕኖ ስር እንዳይወድቅ በንቃትና በጥንቃቄ መጠበቅ የትውልድ አደራ ነው፡፡ እንዲሁም ብርቅዬ ባህላዊ እሴቶታችን በሚገባ ተጠብቀውና ተሰንደው ለቀጣዩ ትውልድ ከነሙሉ ክብሩማስተላለፍ ኃላፊነት የሁሉም ነው፡፡ በዚህ ረገድ በክልልና በፌዴራል ያሉ ተቋማት የምርምር ተቋማት ፍቼ ጫምበላላን ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፉበት ሳይንሳዊ ምክረ ሃሳቦችን ሊያቀርቡ ይገባል፣ ልጆችም ይህ ጥበባዊ እሴቶችን በውስጣቸው ይዘው ሊያድጉ ይገባል፡፡ ትምህርትና ስልጠናዎችም እንዲህ ዓይነት መገለጫዎችን ባካተተ መልኩ እንዲቀረጹ ሊደረግ ይገባል፡፡

ይሄንን ያውቁ ኖሯል?

በሲዳማ ዘመን መቁጠሪያ ወይም ካላንደር ውስጥ አንድ ወር ሰባት ሳምንታት አሉት፤ አንድ ሳምንት 4 ቀን ያለው ሲሆን ቀናቱም Dikko, Deela, Qawaadoo እና Qawalanka ይባላሉ፡፡ እንዲሁም እያንዳንዱ ወር 28 ቀናት ያሉት ሲሆን፣ 12ኛው ወር 29 ቀናት አሉት፡፡ ሌላው የሲዳማን ዘመን አቆጣጠርን ልዩ የሚያደርገው በወር ውስጥ የሚገኙ 28ቱም ቀናት የየራሳቸው ስያሜ ወይም ትርጉም አላቸው፡፡ እነዚህም በቅደም ተከተል፡- Argaajjima,  Arba, Bolla, Basa Ama, Basa Beetto, Carroowa, Dureette, DullatteDullatte Beetto, Bidirsa, Deette Beetto, Karaawicha, Gardaaduma, Sonsa, Rurruma, Lumaasa, Gidaada, Ruuda, Ereere Ama, Ereere Beetto, Adula Ama, Adula Beetto, Harfatto, Deette Ama, Dullatte Ama, Bita, Ciico, እና  Sorsa. በመባል ይታወቃሉ፡፡